ኢንስትራክተር ካሳሁን ተካ
ትውልዱ ደብረ ማርቆስ ቢሆንም ከአራት አመታት በላይ አልኖረባትም፡፡ የወታደር ልጅ ስለነበር የመኖሪያ ቦታ መቀያየርን በልጅነት እድሜው አይቶታል፡፡ አዲስ አበባ የቄስ ትምህርት ቤት ዳዊት ደግሞ፣ በተስፋ ኮኮብ ትምህርት ቤት የቀለም ትምህርት ተዋውቋል፡፡ የእግርኳስ መክሊቱን ያገኘበት ግን ሽመልስ ሀብቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር፡፡
በወቅቱ ጎበዝ ተማሪም፣ ጎበዝ ኳስ ተጫዋችም እንደነበር የሚነገርለት ካሳሁን ተካ በዘመኑ ተወዳጅ በነበረው የትምህርት ቤቶች የእርስ በርስ ውድድር ላይ የብዙዎችን እይታ ማግኘት ችሏል፡፡ የመጀመሪያ ክለቡ ጠመንጃ ያዥ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሁለተኛ ዲቪዥዮን ለሚጫዎተው ጠመንጃ ያዥ የወጣቱ ካሳሁን ተካ መምጣት የቡድኑን ደጋፊዎች በእጥፍ የጨመረና የአሸናፊነት ጉዞ ያስቀጠለ ነበር፡፡
ካሳሁን ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተመረጠው ገና የ21 አመት ወጣት ሳለ፣ በሁለተኛው ዲቪዢዮን ለጠመንጃ ያዥ እየተጫወተ መሆኑ አስገራሚ የታሪክ አጋጣሚ ነበር፡፡ በካሳሁን ብስለት የተሞላበት አጨዋዎት የተማረከው ሉቻኖ ቫሳሎ ወደ ኮተን ሊወስደው እንደሚፈልግ የገለፀበትን አጋጣሚ ያስታውሰዋል፡፡ አይቼው የማላውቀውን ብር ከኪሱ አውጥቶ ሰጠኝ የሚለው ካሳሁን ልቡን ለማሸፈት 100 ብር በቂ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ክፍያው 250 ብር መሆኑን የሚናገረው ካሳሁን ይህም ይበዛብኛል ማለቱን ያስታውሳል፡፡ ከገንዘብ ይልቅ የመጫዎት ፍላጎትን ማስቀደም የዚያ ዘመን ልዩ መገለጫዎች ነበሩ፡፡
የሉቻኖ የስልጠና መንገድ ከባድና ሁሉን አቀፍ መሆኑ የእግርኳስ ህይዎቱን በመልካም አጋጣሚዎች የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ የአሰልጣኙ ከኮተን መውጣት ለካሳሁን ኳስ ወደ ጀመረባት አዲስ አበባ እንዲመለስና ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን እንዲቀላቀል ምክንያት ነበር፡፡ የኢሰማ ቡድኖች ሲፈጠሩ ደግሞ ወደ ፊት ቀጣይ መዳረሻው ነበር፡፡
የሀገሩን መለያ ለብሶ የመጀመሪያ ጨዋታን ያደረገው ከ ዛምቢያ ጋር ሲሆን የ10ኛውኛ እና የ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሀገሩን ወክሎ ተጫውቷል፡፡ ለሁለት አስርት አመታት በወጥነት 5 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ የነበረ በክለብ ደረጃም ብዙ ዋንጫዎችን ያገኘ የሀገር ባለታሪክ ነው፡፡
እየተጫወተ የአሰልጣኝነት ኮርሶችን የወሰደው ካሳሁን ተካ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸው አቃቂ ጨርቃ ጨርቅና ቃጫ ቡድኖች ነበሩ፡፡ በመድህን በቅዱስ ጊዮርጊስና መብራት ኃይል ኢትኮባና ሙገር የተሳኩ ጊዚያትን አሳልፏል፡፡ ወደ ምስራቅና ምዕራብ ጀርመን በመጓዝም የስልጠና መንገዱን አዳብሯል፡፡ ከመንግስቱ ወርቁ በኃላ የካፍ ኢንስትራክተር በመሆን በኢትዮጵያ ውስጥና በበርካታ የአፍሪካ ሀገሮችም እየተጓዘ ልምዱን አጋርቷል፡፡ በፌዴሬሽኑ ውስጥም በአመራርነትን ያገለገለ ባለሙያም ጭምር ነው:: የኢትዮጵያ ወጣትና ዋና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ በመሆንም ሀገሩን አገልግሏል፡፡ ተጨዋቾች ጣሊያን ላይ ሲጠፉ ሜዳ ውስጥ ገብቶ ከሞሮኮ ጋር የተጫወተ አሰልጣኝ ጭምር ነው፡፡
የኢንስትራክተር ካሳሁን ተካ የረዥም አመታት የእግር ኳስ ጉዞ እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ተጠቅሰው የማያልቁ ስኬቶችን በተጫዋችነትም፣ በአሰልጣኝነትም ያገኘ የሀገር ባለውለታ ጭምር ነው፡፡ ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ በስልጠና የዳበረ የሙያ ባለቤት ጭምር ነው፡፡ አሁን ላይ በሀገረ አሜሪካ ኑሮውን ያደረገው ይህ ባለታሪክ የሰራውን ያህል እውቅና ያልተሰጠው፣ በቅጡም ያልተመሰገነ በመሆኑ በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያውያን ስፓርትና ባህል ፌዴሬሽን በዘንድሮው አመት ሮም ጣሊያን ላይ በሚደረገው ውድድር ላይ የክብር እንግዳ በማድረግ ተገቢውን እውቅና በመስጠት ሊያመሰግነው ተዘጋጅቷል፡፡
በ አረጋ ከፈለው
በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባህል ፌዴሬሽን
የክብር እንግዳችን ኢንስትራክተር ካሳሁን ተካ
