

21ኛው የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባህል ፌስቲቫል ባሳለፍነው ሳምንት በሮም ከተማ መካሄዱ ይታወቃል። በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቀውና በአውሮፓ ውስጥ ለኢትዮጵያውያንና ለትውልደ ኢትዮጵያውያን የመገናኛ፣ የስፖርት፣ የባህልና የአንድነት ልዩ መድረክ የሆነው ይህ ፌስቲቫል፣ ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ረጅም ርቀት ተጉዘው በመጡ ተሳታፊዎች ላይ በደረሱ አሳዛኝና ኢትዮጵያዊነትን በማይመጥኑ ተግባራት ተጠናቋል። በመጀመሪያ፣ በዚህ ፌስቲቫል ላይ ለመሳተፍ መጥታችሁ ላልተፈለገ እንግልት፣ ችግርና ከፍተኛ ወጪ የተዳረጋችሁ ተሳታፊዎቻችን በሙሉ፣ በ ESCFE ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስም ከልብ ይቅርታ እንጠይቃለን። ለተፈጠረው ሁኔታም ሙሉ ኃላፊነት የምንወስድ መሆኑን እናሳውቃለን። ፌዴሬሽኑ ፌስቲቫሉ ከመካሄዱ ወራት አስቀድሞ፣ የግል ጥቅማቸውን በሚያሳድዱ የተደራጁ ግለሰቦች የተፈጠሩ በርካታ ተግዳሮቶችን ሲያስተናግድ ቆይቷል። ሆኖም ፌዴሬሽኑ ይህንን ታላቅ የኢትዮጵያውያን መገናኛ መድረክ ከመሰረዝ ይልቅ፣ ችግሮችን በትዕግሥትና በሆደ ሰፊነት ተቋቁሞ ለማካሄድ መርጧል። ይህን ውሳኔ የወሰድነው፣ ብዙ ተሳታፊዎች የትራንስፖርትና የሆቴል ወጪያቸውን አስቀድመው በማውጣታቸው፣ የዕረፍት ጊዜያቸውንም ለዚህ መርሃ ግብር በመገኘት ለማሳለፍ አስቀድመው በማስተካከላቸው፣ እንዲሁም ፌስቲቫሉን በጉጉት ሲጠብቁ የነበሩ ታዳጊዎችና ወጣቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ሆኖም ግን፣ ከአዘጋጁ ኢትዮ ሮማ ተወካይ ጀምሮ በግልም ሆነ በቡድን የተደራጁ ሌሎች አካላት ዝግጅቱ እንዲበላሽ፣ ተሳታፊዎቻችን የበለጠ እንግልት እንዲደርስባቸው ያደረጉ በርካታ ክስተቶችን ፈጥረዋል። ከእነዚህም መካከል ደረጃውን ያልጠበቀና ለዚህ ዓይነት ዝግጅት የማይመጥን ቦታ መምረጥ፣ የፌዴሬሽኑን ፕሬዚዳንትን ጨምሮ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን ስራቸው በአግባቡ እንዳያከናውኑ የስራ እገታ ማድረግ፣ የመብራትና የውሃ አገልግሎቶች ማቋረጥ እና በዚህም አገልግሎት ሰጪዎችንና ተሳታፊዎችን ማሳዘን ይገኙበታል። በተጨማሪም፣ “አርቲስቶች ክፍያ አልተፈጸመላቸውም” የሚሉና ሌሎችም ከእውነት የራቁ አሉባልታዎችን በማሰራጨት የፌዴሬሽኑን ስም ለማጥፋት የተደረጉ ጥረቶች ኢትዮጵያዊነትን በማይወክል መልኩ የተፈፀሙ አሳዛኝ ተግባራት ናቸው። በተለይም ለዚህ ፌስቲቫል ከተለያዩ የአውሮፓ አገራት ረጅም ርቀት ተጉዘው የመጡ ወገኖቻችን የገጠማቸው እንግልትና ኪሳራ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም። ፌዴሬሽኑ ሕጋዊ እውቅና ያለው፣ ገቢና ወጪውን በኦዲት የሚያስመረምር፣ ከማንኛውም የፖለቲካ ተቋም ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ለመወከልና ለማገልገል የቆመ ተቋም ነው። ሆኖም ግን “እኛ ብቻ እንወስናለን” በሚል አስተሳሰብ በተደራጁ ግለሰቦች የፌዴሬሽኑን ሕጋዊና ተቋማዊ ሥርዓት ለማፍረስና ለማዳከም የተደረጉ ጥረቶች ሁላችንንም ያሳዘኑ ክስተቶች ሆነው አልፈዋል። ከሰሞኑም ፌዴሬሽኑን ለማጥላላትና ስሙን ለማጥፋት በቲክቶክና በሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች የተከፈተውን የስም ማጥፋት ዘመቻ በጥንቃቄ እየተከታተልን ነው። ሆኖም ፌዴሬሽኑ ከማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን ግላዊ ጥቅም በላይ የኢትዮጵያውያንን አንድነት፣ ባህልና የጋራ ጥቅም በማስቀደም ሥራውን በቁርጠኝነት ይቀጥላል። ፌዴሬሽኑ በቀጣይ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴውን አስቸኳይ ጉባኤ በመጥራት፣ በፌስቲቫሉ ዙሪያ የተከሰቱትን ሁሉንም ጉዳዮች በግልጽነት እንደሚመረምር፣ እውነታውንም በመረጃ አስደግፎ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ እናሳውቃለን። በመጨረሻም፣ ይህ ፌስቲቫል የአንድ ግለሰብ፣ የአንድ ቡድን ወይም የአንድ አካባቢ ንብረት አይደለም። የ21 ዓመታት ታሪክ ያለው የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ ነው። ይህንን ታላቅ ተቋም ከግል ጥቅም፣ ከመከፋፈልና ከግጭት በላይ በማስቀመጥ፣ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ሁላችንም የየራሳችንን ኃላፊነት እንድንወጣ እንጠይቃለን። እውነት በጊዜው ይገለጣል፤ ሕዝብም በእውነታው ይፈርዳል! በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባህል ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ





