ሮማ ታሪካዊ ከተማ፤ መጠንቀቅ እንጂ መቆም መፍትሔ አይሆንም፤፤

በመጀመሪያ በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባህል ፌድሬሽን የከበረ ሰላምታውን እያቀረበ በመቀጠልም የፍጡራን ሁሉ የበላይ አምላክ ለአገራችን ሰላም፣ መረጋጋትና ብልፅግና ፤ለመሪዎቻችን መልካም ሕሊና፤ ለሕዝባችን በአንድነትና በጋራ የመኖርን ልቦናን ይሰጥልን ዘንድ የዘወትር ምኞታችንና ፀሎታችን ይሆናል። በመቀጠልም ይህ የስፖርትና ባህል ፌድሬሽን ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ብሎም የኢትዮጵያ ወዳጆችን በልዩነት ነገር ግን ሊያግባባንና በሚያስተሳስረን ኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ላለፉት 14 ዓመታት ስፖርትና ባህልን ብቻ ማዕከል ያደረገ ስራዎችን ሲሰራና በተለይም ኢትዮጵያዊ ማህብረሰባችን በእጅጉ ያሳተፈና መልካም አጋጣሚ ሆኖም ለሰዎች በትዳር መተሳሰር ምክንያት የሆነ፤ አልፎ ተርፎም ልጆቻቸው በፌድሬሽኑ ዝግጅት ላይ መሳተፍ የጀመሩና የፌድሬሽኑ ውጤቶች ሆነዋል፤ እነዚህንም የዛሬ ልጆች የነገ ተረካቢን ወጣቶች ማንነታቸውን ብሎም ስለ ኢትዮጵያዊነት በሚወደስበትና ደምቆ በሚታይበት መድረክ ውስጥ ተኮትኩተው የሚያድጉበትን፣ ኢትዮጲያዊነትን ጠንቅቀው የሚረዱበትን፣ብሎም አጥብቀውም የሚይዙበትን መንገዶችን ከማመቻቸት ውጭ አማራጭ የለንም። ከዚህ በመነሳትና የፌድሬሽኑን ራዕይ ከግብ እንዲደርስ ለማድረግ መጠንቀቅ እንጂ መቆም መፍትሄ እንዳልሆነ ሁሉ ፌድሬሽኑም ካለፈው ችግሮችና ስህተቶች በመማር መቀጠል ግድ እንደመሆን መጠን ይህም ማህበረሰቡን የማሰባሰብ መልካም ዓላማ ዘንድሮ ቀጥሎም 15ኛ ዓመት በዓሉን በሮማ ከተማ በደመቀና ከመቼውም ጊዜ በበለጠና ባማረ ሁኔታ ለማክበር በከፍተኛ ዝግጅት እየጠበቅናችሁ እንደምንገኝ ስናሳውቅ በታላቅ ደስታና ኩራት ይሆናል።

ይህ የስፖርትና ባህል ፌድሬሽን በብዙ ውጣ ወረዶች ውስጥ ያለፈና አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ቢገኝም ትናንትም ሆነ ዛሬም ፈታኝ ሁኔታዎች በየጊዜው አይነታቸውን እየቀያየሩም ብቅ እያሉ ይታያሉም። ያሳለፍናቸው ወጣ ውረዶችና አሁንም እያለፍንባቸው ያሉትን ሁኔታዎች ስንገመግም የዓለም መጨረሻ መቃረቢያ ምልክት ይመስላል፤ ራስን ማክበርና ህሊናን መፍራት የቀረበት ዘመን ላይ ደርሰናል፤ ግብዞች የበዙባት ከእውነት የራቀን የሃሰት ደባቸውን መርዝ አሳምረው የሚረጩባት የቲያትር ዓለም ሆናለችም፣ ልጅና አዋቂው፣ ጎልማሳና አንጋፋው፣ መሪና ተመሪው የማስተዋል ህሊናው ከላዩ ተገፎ እርቃኑን ይታያል፤ ወደ አውሬነቱም የተመለሰ ይመስላል፤ ጠንካራ ነኝ ባዩ ጉልበት የከዳውን ሲደቁሰው፣ ሲደረምሰው ብሎም ሲደመስሰው ይታያል፤ ጊዜና ጉልበቱንም ተጠቅሞ ያለስም ስምን፣ ያለስራው ዝናና ክብርን ብሎም ዙፋን ደፍቶ ይታያል፤ እውቀቱ ሳይኖር አዋቂነት፣ ባዶ ሆኖ ሳለ ክብደት (የከበደ መስሎ መታየት)፣ ከመስራት አፈ ጮሌነት፤ የሚሰራን ማጥላላት ብሎም አከርካሪን ማለት ዘመኑ ያመጣው ፈሊጥና ልማድም ሆኖ በእጅጉ በአለማችን ላይ ተንሰራፍቶ ይታያል። ምድራችንም የሰዎች መታወክና ግራ መጋባትም እርካታቸው በሆነና እጅግ ሃላፊነት በጎደላቸው የሰው ዘር ተብዮች ወጥመድ ስር ወድቃ ትገኛለችም፤ የሰውነት መገለጫነት በሌለው መሳሪያቸው (አፈጮሌ ምላሳቸውም) በየጊዜው በሚረጨው መርዛማ ሴራም የሰው ዘርም ግራ ተጋብቷል፤ ግራ ከመጋባትም አልፎ አዕምሮም ታውኳል፤ ከመታወክም አልፎ በየጊዜው በሚታዩት አፀያፊና ስነ ምግባር በጎደላቸው ምግባሮችም ውስጡ ደምቶና ልቡም ተሰብሮ ይታያል፤ አስተዋይነቱንም ነጥቀውታል፤ ከዚህም የተነሳ ወደ ኋላና ፊቱ፣ ቀኝና ግራውን እንዳይመለከትና ፍርድን፣ ዳኝነትን ቆም ብሎ፣ አመዛዝኖና አስተውሎ ከመስጠት ይልቅ በተነገረውና በደሰረበት ቦታ ላይ ሆኖ መስጠት በእጅጉ ተንሰራፍቶ ይታያል፤ ይህም እንኳን እንደእኛ ላለው በጋራ የመስራት ልምድ ላነሰው ህብረተሰብ ክፍል ቀርቶ አድገናል፣ በልፅገናል ለሚሉትም ህዝቦች ግራ እያጋባ ያለና ወደ አደገኛ የትውልድ ክስረት የሚያመራ፤ ፀረ- ህብረት ሆኖ ይገኛል።

እንግዲህ ምርጫው ለየቅል፣ለየራስ ይሆናል፤ እንደዘመኑ ሰው አውሬ ሆኖ ተበላልቶና ከንቱ ሆኖ መቅረት? ወይንም እንደ መልካሙ የሰው ዘር መቻቻልን፣ ይቅር ባይነትን ለብዙሃንም የሚያስብን ሆኖ መገኘትና ሰፋ ያለ ዘላቂነት ያለውን መንገድ ማስቀደሙ ይበጃል? ይህ የማህበረሰባችን ስብስብ ቀጣይነቱን ሁላችንም ባይሆን እንኳን አብዛኞቻችን ስለምናምንበትም፤ በእኛ ብቸኛ አማራጭ የምንለው እንደ መልካሙ የሰው ዘር መልካም አመለካከትን የተላበሰና ለብዙሃንም የሚያስብን ሆኖ መገኘት ነው። ምክንያቱም መልካም አመለካከት መልካም ስራን፤ መልካም ስራም መልካም ትውልድን ይፈጥራልና ነው።

በመጨረሻም፤ ምንም እንኳን ሰዎችን ሁሉ ማስደሰት ባይቻልና ስር ነቀል ለውጥን ማምጣት ባንችል ባገኘነው አጋጣሚ በመጠቀም መሰረትን መጣልና ጉዞን መጀመር ይቻላልና የዘገየ ቢመስልም ነገን የተሻለና ህብረተሰባችንን ወደ ተሻለ የአመለካከት ለውጥ ማዘጋጃ መድረክ መፍጠር ብሎም ካዛም ባለፈ የጋራችን በሆነ ሁኔታዎች ላይም በጋራ የመስራት አመለካከት እንዲሰርፅ መስራት ይቻላል፤ ያስፈልጋል። ውጤቱ ምን ይሆናል የሚለውን በእርግጠኝነት መናገር አዳጋች ቢሆንም ነገር ግን አጋጣሚው ግን መልካም ነው ብሎ ፌድሬሽኑ ያምናል፤ ካሳለፍናቸው ተሞክሮዎች በመነሳት ሁኔታው ጥቁር ድንጋይ ላይ ውሃ ማፍሰስ ቢሆንምና ተስፋ አስቆራጭ ቢመስልም ዛሬን እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀምና መስራት ብሎም ምሳሌ መሆን ያስፈልጋል። ይህም በጋራ የመስራት የአስተሳሰብ ለውጥን ስሜት ይፈጥርልናል፤ይህን ማድረግ ስንችል በትዕግስትና በመቻቻል አጥር የታጠረ የብዙሃን ስሜትን የሚያስጠብቅ አመለካከት በውስጣችን እንዲሰርፅ፤ ብሎም መዳበርም ይጀምራል፤ይህም ማለት ደግሞ ሰዎች ሁሉ አመለካከታችን ሁሉ አንድ ይሁን ማለት ሳይሆን ነገር ግን በአለን አመለካከትና ልዩነት በጋራ የመመካከርና የመስራትን ባህልና ልምድ ማዳበር ስንችል የግል ፍላጎትና ስሜት በብዙሃን ፍላጎት እየተተካና እየተለወጠ ይመጣና ጉዞዋችን ቀጣይነት እንዲኖረው መንገዱ ቀና ይሆናል። ይህን ማድረግ ከቻልን መሻሻልና ለውጥ አለ፤ መሻሻል ካለ የዕድገት መንገድ አለ፤ ዕድገት ካለ ለሎች የደረሱበት ደረጃ ላይ መድረስ ይቻላል።

ኃይላችን ሕብረታችን ነው! በሕብረትም የነገን ትውልድ ማዘጋጀት ይቻላል፤
በአውሮፓ የኢትዮጵያ ስፖርትና ባህል ፌድሬሽን